ጨረቃ
From Wikipedia, the free encyclopedia
ጨረቃ (ምልክት፦) የመሬት ብቸኛዋ ሳተላይት ስትሆን በሥርዓተ-ፀሐይ ውስጥ አምስተኛ ትልቅ ሳተላይት ናት። ከመሬት መሀል እስከ ጨረቃ መሀል ድረስ ያለው አማካይ ርቀት 384,403 ኪ.ሜ. (238,857 ማይል) ያህል ነው። ይህ ርቀት ከመሬት አንድ ጫፍ እስከ ሌላኛው ተቃራኒ ጫፍ (diameter) ያለውን ርቀት ሰላሳ (30X) ይበልጣል። ሁለቱ አካላት ሥርዓታቸውን የሚጠብቁበት ማዕከላዊ ነጥብ 1,700 ኪ.ሜ. (1,100 ማይል) ማለትም የመሬትን ራዲየስ አንድ አራተኛ (1/4) ከመሬት ጠለል ዝቅ ብሎ ይገኛል። ጨረቃ በመሬት ዙሪያ በየ27.3 ቀናት አንድ ሙሉ ዙር ታጠናቅቃለች። ይህም መዞር ለጨረቃ በየ29.5 ቀናት የሞላና የጎደለ መመልክ መያዝ ዋና ምክንያት ነው። የጨረቃ ከአንድ ጫፍ እስከ ሌላኛው ተቃራኒ ጫፍ (diameter) ያለው ርቀት 3,474 ኪሜ (2,159 ማይል) ሲሆን ከመሬት ተመሳሳይ አንድ አራተኛ (1/4 X የመሬት ዲያሜትር) በትንሽ ይበልጣል። የመሬትን አንድ አራተኛ ስፋት ሲኖራት ይዘቷ (volume) ግን የመሬትን ሁለት በመቶ (2%) ብቻ ነው። የጨረቃ ስበት የመሬት ስበትን አስራ ሰባት በመቶ (17%) ጋር ይነጻፀራል። ጨረቃ የሰው ልጅ ያረፈባት ብቸኛዋ የጠፈር አካል ናት።
በ2011 የቻይና ሕዝባዊ ሪፐብሊክ ሳይንቲስቶች ሮቦቶችን ወደ ጨረቃ ልከው የጎመንዘር አይነት (Brassica napus)፣ የድንችና የጥጥ ዘሮችን በጨረቃ ላይ በመያያዣ ውስጥ ማብቀል እንደተቻለ አስረዱ። ወደፊት ሰዎች ወደ ጨረቃ ቢመልሱ ኖሮ፣ በነዚህ ሦስት ምርቶች፦ ጎመንዘር ለዘይት፣ ድንች ለምግብ፣ ጥጥም ለልብስ፦ እንደሚረዷቸው አሉ። እንዲሁም የድንጋይ ፌጦ (Arabidopsus spp)፣ እርሾና የፍራፍሬ ዝንብ በሙከራው ውስጥ እየታደጉ ነበር። ሆኖም ከ፫ ቀን በኋላ ናሙናዎቹ ሁሉ ከጨረቃ አየር ሙቀት የተነሣ በርደው አርፈው ነበር።