ማልትኛ
From Wikipedia, the free encyclopedia
ማልትኛ የሴማዊ ቋንቋዎች ቤተሠብ አባል ነው። በሜድትራኒያን ባሕር ውስጥ በሚገኘው ደሴት አገር በማልታ ላይ ይናገራል። መንስኤው ከቅርብ ዘመዱ ከአረብኛ ነው። ከሁሉ የሚመስለው የቱኒዚያ አረብኛ ሆኖም ከማልታ ቅርብ ጊዜ ታሪክ የተነሣ ብዙ ቃላትና ድምጽ ከጣልኛ እና ከእንግሊዝኛ ወስዷል።
ከሴማውያን ቋንቋዎች ሁሉ ማልትኛ ብቻ በላቲን አልፋቤት የተጻፈ ነው። በ1928 ዓ.ም. ማልትኛና እንግሊዝኛ የደሴቱ መደበኛ ቋንቋዎች ተደረጉ። ከዚያ ዓመት በፊት መደበኛው ቋንቋ ጣልኛ ነበር። ዛሬ የተናጋሪዎቹ ቁጥር 371,900 ነው። ከነዚህም ውስጥ በአውስትራሊያ፥ አሜሪካና ካናዳ የሚችሉት ይገኛሉ።
በማልትኛ ከሁሉ መጀመርያው ሰነድ በ1460 ዓ.ም. አካባቢ በፔትሮ ካሻሮ የተቃኘው ግጥም ካንቲሌና ነው። ይሁንና ለረጅም ዘመን ማልትኛው ስነ-ጽሑፋዊ ሳይሆን በብዛት የመነጋገርያ ቋንቋ ነበርና ጽሕፈት የተደረገው በአረብኛ በኋላም በጣልኛ ነበር።