ግስበት
From Wikipedia, the free encyclopedia
ግስበት ማናቸውም ግዝፈት ያላቸው ቁስ ነገሮች እርስ በርሳቸው እንዲሳሳቡ ግድ የሚላቸው የተፈጥሮ ጉልበት ነው። በዕለት ተለት ኑሯችን ግዝፈት ያላቸው ነገሮች በአየር ከመንሳፈፍ ይልቅ ከመሬት ጋር እንዲላተሙ የሚያደረጋቸው፣ በሌላ አነጋገር ለነገሮች ክብደት የሚሰጣቸው ግስበት ነው። የመሬት ግስበት ወይም በተለምዶ የመሬት ስበት መሬት ባላት ግዝፈት ምክንያት ሌላ ግዝፈት ያለውን ነገር የምትስብበት የተፈጥሮ ጉልበቷ ነው። ጨረቃ ከመሬት በራ የማትጠፋው የመሬት ግስበት አንቆ ስለያዛት ነው። ሜርኩሪን፣ ቬነስን፣ ሌሎች የተቀሩትን ፈለኮችን በፀሐይ ዙሪያ ጠፍሮ ከምህዋራቸው በረው እንዳይጠፉ የሚያደርጋቸው የፀሐይ ግስበት ነው። ከዋክብትንና ሌሎች ግዙፍ ቁሶችን በየረጨታቸው መድቦ አስተቃቅፎ የሚይዛቸው ይኽው መሰረታዊ ጉልበት ነው። ግስበት፣ ባጠቃላይ መልኩ ፣ በጥልቁ ጠፈር ውስጥ ተበትኖ የሚገኘውን ቁስ እንዲጓጉል ያደርጋል። ከዚህ አንጻር ለመሬት፣ ለተስፈንጣሪ ከዋክብት፣ ለ ፈለኮች (ፕላኔቶች) ፣ ለከዋክብት፣ ለረጨቶችና መሰል ግዙፍ አካላት ጓጉሎ መፈጠርና ቀጣይ ህልውና ይህ ጉልበት አስፈላጊና በርግጥም መሰረታዊ ነው ፤ አለበለዚያ የመጓጎልና አንድ ሁነው የመቀጠል እድል አይገጥማቸውም ነበርና። በውቅያኖሶች ለሚፈጠሩ ማዕበሎች፣ ለወንዞች መፍሰስ፣ ለአዳዲስ ከዋክብትና ፈለኮች ውስጣው ከፍተኛ ሙቀት እና ሌሎች ህልቁ መሳፍርት ክስተቶች ተጠያቂ ጉልበት ነው።