ውክፔዲያ
From Wikipedia, the free encyclopedia
ውኪፒዲያ የባለ ብዙ ቋንቋ የተሟላ ትክክለኛና ነጻ መዝገበ ዕውቀት (ኢንሳይክሎፒዲያ) ነው። ማንኛውም ሰው ለውኪፒዲያ መጻፍ ይችላል። ውኪፒዲያ፣ ውኪሚዲያ የተባለ ግብረ ሠናይ ድርጅት ከሚያካሂዳቸው ፕሮግራሞች አንዱ ነው። ወደ 272 በሚጠጉ የተለያዩ ቋንቋዎች ፅሁፎች አሉት። ውኪፒዲያ በኢንተርኔት ከሚገኙ ታዋቂ መዛግብተ ዕውቀት አንዱ ነው።
ውኪፒዲያ ድረ-ገፅን መሰረት ያደረገና ማንም ሰው በቀላሉ እንዲያስተካክለው ተደረጎ የተዘጋጀ፣ በብዙ ቋንቋዎች የሚቀርብ ነጻ የኢንተርኔት መዝገበ እውቀት ወይም ኢንሳይክሎፒድያ ነው። ውኪፒዲያ የሚለውን ስያሜ ያገኘው “ዊኪ” (ትርጉሙ ፈጣን ማለት ነው) የሚለውን ቃል ከሀዋይኛ ቋንቋ በመወሰድና “ኢንሳይክሎፒድያ” ከሚልው የእንግሊዘኛ ቃል ጋር በማዳቀል[1] ሲሆን እያንዳንዱ የውኪፒዲያ ገጽ እራሱ ከሚይዘው መረጃ በተጨማሪ አንባቢን ይበልጥ ግነዛቤ ለማስጨበጥ ከሚረዱ ሌሎች ተዣማጅ ገፆች ጋር ያለውን የትስስር መረጃም በተጨማሪነት አካቶ የያዘ ነው።
ውኪፒዲያ የተመዘገበ (የሚታወቅ) አድራሻ ሳይኖራቸው ኢንተርኔት ላይ ያለምንም ክፍያ በፈቃደኝነት የሚጽፉ የበርካታ ግለሰቦች የጋራ የትብብር ውጤት ነው። ስለሆነም ከአንዳንድ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ገደብ ከተጣለባቸው ገጾች በስተቀር ማንኛውም የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚና ፈቃደኛ የሆነ ሰው፤ በብዕር ስም፣ ትክለኛ ስምን በመጠቀም ወይም ደግሞ ያለምንም ስምና አድራሻ፣ ውኪፒዲያ ላይ የፈለገውን ሀሳብ የማስፈርና አስተዋጾ የማድረግ አሊያም ቀድሞ በሰፈረ ጽሁፍ ላይ ተጨማሪ መረጃን የማካታት፣ ስህተትን የማረምና የማስተካከል ፈቃድ ተሰጥቶታል።[2]
ውኪፒዲያ ከተመሰረተበት ከ2001 እ.ኤ.አ. ጀምሮ በፍጥነት በማደግ ላይ ያለና በብዛት ከሚጎበኙና ኢንተርኔት ላይ ከሚገኙ በረካታ የማጣቀሻ ድረ-ገጾች መካከል አንዱ ሲሆን 2011 እ.ኤ.አ. መጋቢት ወር ብቻ ከ400 ሚሊዎን በላይ አዳዲስ ጎብኝዎች ድረገጹን እንደጎበኙት ኮም ስኮር ያካሄደው የጥናተ ዘገባ ያመለክታል። ውኪፒዲያ ከ82,000 በላይ አርታኢዎች፣ ከ270 በላይ በሚሆኑ ቋንቋዎች ያጠናቀሯቸውን ከ19,000,000 በላይ የሚሆኑ መጣጥፎችን አካቶ የያዘ ድረ-ገጽ ነው። ውኪፒዲያ በአሁኑ ጊዜ 3,874,529 የእንግሊዘኛ መጣጥፎችን የያዘ ሲሆን በየቀኑ ከመቶ ሺህ በላይ ጎብኝዎች እንደሚጎበኙትም ይገመታል። በተጨማሪም በተለያዬ የአለም ክፍል የሚኖሩ ግለሰቦች በሚያደርጉት የጋራ አስተዋጽኦ በየቀኑ ከአስር ሺህ በላይ መጣጥፎች የተለያዩ ማስተካከያዎች የሚደረግባቸው ሲሆን ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ መጣጥፎች ደግሞ ውኪፒዲያን በየቀኑ ይቀላቀላሉ።[3]
ምንም እንኳን መሰረታዊ የውኪፒዲያ መርሆች የሚባሉት አምስት ቢሆኑም ይህንኑ መዝገበ-ዕውቀት (ኢንሳይክሎፒዲያ) ይበልጥ ለማሻሻልና ለማጎልበት የሚያግዙ ሌሎች በርካታ ፖሊሲዎችና መመሪያዎች በውኪፒዲያ ማህበረሰብ ተቀርጸው ተግባር ላይ የዋሉ ሲሆን ነገር ግን እነዚህን መሰረታዊ መመሪያዎችና ደንቦች አስተዋጾ ማድረግ ካልጀመረ በስተቀር ማንኛውም ሰው የማወቅ ግደታ የለበትም።[4]
በሌላ በኩል፣ ውኪፒዲያ አንድ ሰው ካለው የሙያ ችሎታ ይልቅ ለሚያበረክተው አስተዋፆ ትልቅ ግምት የሚሰጥ በመሆኑ፣ በተለያየ የእድሜ ክልል፣ ባህልና መነሻ (ዳራ) የሚገኝ ማንኛውም ሰው የውኪፒዲያ አስገዳጅ ፖሊሲዎችን አሟልቶ እስከተገኘ ድረስ፣ ውኪፒዲያ ላይ የፈለገውን መጣጥፍ እንዳንድስ የመጨመር አሊያም ማንኛውም ውኪፒዲያ ላይ የሚገኝ ሌላ ጽሑፍ፣ ማጣቀሻና ምስል የማየት የማሻሻልና የማረም አንዳደም ሙሉ ለሙሉ የመለዎጥና ፈቃድ አለው። በመሆኑም ውኪፒዲያ በተለያዩ አስተዋጾ አድራጎዎች በየጊዜው ማሻሻያ የሚደረግበት እንደመሆኑ መጠን፣ አዲስ ከሚካተቱት መጣጥፎች ይልቅ ቀደም ሲል በድረ ገጹ የተካተቱ መጣጥፎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየታረሙና እየተሻሻሉ የሚሄዱ በመሆናቸው የተሻለ የሐሳብ ጥራት፣ የመረጃ ሚዛናዊነትና ምሉእነት እንደሚኖራቸው ይታመናል።